በጀርመን አገር በሙኒክ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፈጣን ምላሽ ለወገኔ በሚል ዝግጅት ከ15,000.00 € (አስራ አምስት ሺህ ዩሮ)በላይ አሰባሰቡ።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአሸባሪው የህውሃት ቡድን እኔ ወደ የመንግስት ስልጣን ካልተመለስኩ ሀገር ትፍረስ በሚል ዕብሪት በቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ሰላማዊው የሀገራች ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ ለመገደል ፣ንብረቱን ለመዘረፍ፣ለመቁሰልና ለመሰደድ መዳረጉን የሰሙ በሀገር ውስጥና ከገር ውጪ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁጭትና ሀዘን ውስጥ ወድቀዋል።
እነዚህ ይህ ቁጭትና ሀዘን እንቅልፍ የነሳቸው በመላው ዓለም የተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በግልና በተለያዩ  መልክ ተደራጅተው የገንዘብ፣ የምግብና የአልባሳት ዕርዳታ ማሰባሰብና ለተጎጂዎች በማድረስ ላይ ሲረባረቡ ይስተዋላል።

የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ በሙኒክና አካባቢው ስር የተደራጁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሌሎች ሀገር ወዳድ ወገኖቻቸው በወቅቱ የሀገራችን ጉዳይ ላይ መክረው በተደራጀ  የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲያቸው አስተባባሪነት የበኩላቸውን ለማድረግ በመነሳሳት ሁለት የዕርዳታ ማሰባቢያ ዕቅዶችን በማስቀመጥ ተንቀሳቅሰዋል።

1ኛው..ሀገርን የማዳን አስቸኳይ ጥሪ  በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ሲሆን።
በየወሩ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ ለሀገርና ለወገን ለመድረስ የሚያስችል  የገንዘብ እርዳታ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ሲሆን
2ኛው.ፈጣን ምላሽ ለተራበው፣ለተጠማውና ለታረዘው ወገኔ !* በሚል መርህ  ላይ የተመሰረተና ሀገር ወዳዶች የሚያደርጉትን በአንድ ጊዜና በአፋጣኝ የሚለግሱትን የገንዘብ ዕርዳታ ማሰባሰብ ነው።
በእነዚህ  በሁለቱም ዕቅዶች መሰረት የተደረገው እንቅስቃሴ እጅግ አመርቂ የሆነ ውጤት መገኘቱን ከዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ሲገልጹ
*ፈጣን ምላሽ ለተራበው፣ለተጠማውና ለታረዘው ወገኔ*
በሚለው መርህ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ በሙኒክ በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የወገን ለወገን ይድረስ ጥሪውን
በኦክቶበር 31.2021 ባዘጋጀው ልዩ ዝግጅት ከ15,000.00€ (አስራ አምስት ሺህ ዩሮ) በላይ ለማሰባሰብ መቻሉንና

በሌላ በኩል በ1ኛ ደረጃ በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ሀገራችን የምትገኝበትንን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ኮሚዪኒቲው ሀገር ወዳድ ወገኖችን በማስተባበር በየወሩ እንደ መነሻ  50€ (ሃምሳ ዩሮ) አየተዋጣ  ለአንድ አመት የሚዘልቅ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ከጀመረ እነሆ ሶስተኛ ወሩን መያዙንና የሚያበረታታ ውጤት እየታየበት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በዚህ ለአንድ አመት የገንዘብ መዋጮ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከዚህ መልዕክት ጋር በተቀመጠው ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀው የባንክ አካውንት በየወሩ የተቻላቸውን ያህል Dauerauftrag ፣ ወይም የአመት፣ ሩብ አመት፣የስድስት ወር በማስተላለፍ  መሳተፍ የሚችሉ መሆኑም በተጨማሪ ተገልጿል።

 ይህ በሙኒክና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ከጥቂት ወራት በፊት *ደግሞ ለአባይ* በሚል ልዪ የግሪል ዝግጅት አዘጋጅቶ የቦንድ ሽያጭና የገንዘብ ልገሳ፣እንዲሁም የምግብና የመጠጥ ሺያጭ በጥቅሉ ከ20,000.00€(ሃያ ሺህ ዩሮ)  በላይ አሰባስቦ ለሚመለከተው ክፍል ማስተላለፉም ተገልጿል።

ከሀገራችንና ከህዝባችን ጎን ለመቆምና እንደ ዜጋ የበኩላችንን ለመወጣት ከህሊናችን በስተቀር የማንንም ፈቃድ ወይም ይሁንታ አያስፈልገንም!!
የህዝባችንን ህይወት ለመታደግ የምናቀርበው ምንም ምክንያት የለንም!!!
ለዚህም የሰላም አባት የሆነው!
ፈጣሪያችን ይረዳናል!


ሀገራችንና ህዝባችንን ፈጣሪ ይባርክ!

ማሳሰቢያ
ከላይ በተገለጹት ሁለት መንገዶች ለሀገርና ለወገን የሚደረግ እርዳታ የአቅማችሁን በማድረግ ሰብአዊና ወገናዊ ሃላፊነታችሁን ለመወጣት የምትፈልጉ ሁሉ ለጉዳዩ የተዘጋጁትን የባንክ መረጃዎችን ከዚህ በታች ያስቀመጥንላችሁ መሆኑን በትህትና እንገልፃለን።