ከመፃህፍት አለም ታላቁ ጥቁር ከተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ

መስፍን ጳውሎስ

ፌብሩዋሪ 7,2020

ጀርመን ሙኒክ

ሰላም ወገኖቼ

የ “ታላቁ ጥቁር ” መፅሐፍ ደረሲ ስለ አፄ ምኒሊክ እንግዳ ተቀባይነት እንድንረዳ

 ከማስረጃ ጋር እንደሚከተለው አቅርበውልናል።

…… በዚሁ ዕለት በወጣው የኒውዮርክ ታይምስ “ስለ ንጉስ ምኒሊክ የተነገረ” (Tells of king Minilik) በሚል ርዕስ ዝርዝር ነገሮችን ሰፋ አድርጎ አስነብቧል። “ኤሊስ ስለአቢሲኒያው ንጉሥ ጉብኝቱ ገለፃ አደረገ”በሚል ጽህፈት ርዕስ የቀረበው ዘገባ “አፍሪካዊው ንጉሥ.,.. ስኪነርንና አሜሪካውያንን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው።”በማለት ይንደረደራል።

“የአቢሲኒያ ንጉሥ ምኒልክን ከእልፍኛቸው ተገኝቶ ለማነጋገር የቻለው የመጀመሪያው አሜሪካዊ ዊሊያም ኤሊስ ስለአፍሪካዊቷ አገርና በውስጧም ስላለው የተፈጥሮ ሀብት ብሩህ ግምት ይዞ በትናንትናው ዕለት…. ተመልሷል።….. “

ሚስተር ኤሊስ ከንጉሱ ዘንድ በነበረ ጊዜ የአሜሪካንን ባንዲራ እያውለበለበ በቅርቡ የሚመጣ የመንግሥት ልዑክ ቡደን እንዳለ ለንጉሡ ነግሯቸዋል።ንጉሱም በጉዳዩ ተደስተው “በእግዚአብሔር ፍቅር እቀበላቸዋለሁ። ከግዛቴ ቆርሰው ለመውሰድ ከማይመኙ አገሮች ሁሉ ግኑኝነት ለመፍጠር የምናፍቀው ነገር ነው” ማለታቸውን ኤሊስ ተናግሯል ።

“ታላቁ ጥቁር ” መፅሐፍ ገፅ 186

ለመሆኑ ኤሊስ ከምኒሊክ ጋር እንዴት አሳለፈ? ራሱ የተናገረውን ከታይምስ አሳጥረን እንመልከት በማለት የታሪክ ተመራማሪውና ደራሲው አቶ ንጉሴ አየለ ይጋብዙናል።

“በኦክቶበር 16 ቀን የአቢሲኒያን መንደር አቋርጬ ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ የንጉስ ምኒሊክ የክብር እንግዳ ነበርኩ ።ከእኔ ጋር አብረውኝ የሄዱት የእህቴ ልጅ….. ነበሩ ።ለእኛ ምቾትና እንክብካቤ ሲባል አስፈላጊው ሁሉ ተደርጎልናል።ለማረፊያችንም የተለየ ግቢ ተዘጋጅቶልናል።:…” ንጉሡን መጀመሪያ በግል አስጠርተውት እንደተገናኙና ለሁለተኛ እንዴት እንዳገኛቸው ሲገልፅ እንዲህ ይላል።

“ለሁለተኛ ጊዜ የተገናኘነው ስለእኔ (ለእኔ) በተጣለው ግብር (at a feast arranged for me) ላይ ነበር ።… መኳንነቶቹን ጨምሮ 7000 የሚሆኑ ዜጎች ጥሬ ስጋ ሲበሉ ለእኔም የተለመደው የአሜሪካ እራት ተዘጋጅቶልኝ ነበር።… “

“ግብሩ የተጣለው በትልቅ አዳራሽ ነበር።የንጉሱ መቀመጫ ስፍራ ከሌላው ህዝብ የሚለይበት መጋረጃ አለው። ንጉሱ ሲበሉ መታየት ስሌለባቸው ነወ። በድንገት ሰው ሁሉ ብድግ አለ።እኔም ተነስቼ ቆንጂት ።ለምን እንደቆሙ ስጠይቅ ንጉሱ እጃቸውን እየታጠቡ ስለሆነ ለአክብሮት መቀቆም የሀገሪቱ ባህል እንደሆነ ተነገረኝ።”

“እራት ላይ ጠጅ የተባለው መጠጥ ይጠጣ ነበር ።እንደ ቢራ የሚጠመቅ ነው።በአዳራሹ ዙሪያ ጠጅ የያዘው ቧንቧ. ተዘርግቷል ።አንድ ሰው መጠጣት ሲፈልግ ካሉት ብዙ የቧንቧ ማውረጃዎች አንዱጋ ሄዶ መጠጡን ይቀዳል።…. “

ውድ ወገኖቼ ይህ በ “ታላቁ ጥቁር ” የተዘረዘረው የምኒሊክ ታሪክ በስሜት ይዞ የሚነጉድና ለማቆም አስቸጋሪ እየሆነ ስለሚሄድ ይረዝማል።

አሁንም ጊዜያችሁን ላለመሻማትና ላለመሰሰልቸት እዚሁ የምኒሊክ “የጠጅ ቧንቧ” ላይ ልተዋችሁ ተገድጃለሁ።

በነገው የኮሚዩኒቲያችን ግብር ላይ ጠጅ በቧንቧ ባይቀርብም ደመቅ ያለ ዝግጅት ላይ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን።

መስፍን ጳውሎስ

ፌብሩዋሪ 28,2020