ከመፃህፍት አለም ታላቁ ጥቁር ከተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ

ሰላም ወገኖች እንዴት ከርማችሇል?

በአለፈው በተከታታይ ከ “ታላቁ ጥቁር “መፅሐፍ የተወሰዱ ቅንጭቦችን ሳካፍላችሁ።

የጀመርነውን የአሜሪካን ፕሬዜዳንት ሩዝቬልት ለአቢሲኒያው የወቅቱ ንጉሰ ነገስት ለዳግማዊ ምኒሊክ ከላኩዋቸው ስጦታዎች አንዱ የፐሬዘዳንት ሩዝቬልት ፎቶግራፍ መሆኑን ተመልክተን ሌሎቹን በሚቀጥለው ብዬ ቃል እንደ መግባቴ

እነሆ ዛሬ የቀሩትን ለመጥቀስ መጥቻለሁ።

ከዚህ ፎቶግራፍ በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴት መንግሥት ለአቢሲኒያው ንጉሥ የተለያዩ ስጦታዎችን በጄኔራል ቆንሱላ ስኪነር በኩል የላከች ሲሆን እነሱንም ደራሲው ከጋዜጦቹ ላይ ለቅመው ይጠቅሷቸዋል።

እንመልከት; ‐

“ቀጥሎ የሚያምር የታይፕ ራይተር (መተየቢያ መሳሪያ )ለንጉስ በተደረጉ ቀረበላቸው ።የአሜሪካን ታይፕ ራይተር ማምረቻ ኩባንያ ለምኒሊክ በስጦታ እንዲሰጥለት ያበረከተው ነበር።ምኒሊክ ታይፕ ራይተሩን በጉጉት ተቀብለው ተመለከቱት።ታይፕ ራይተሩ የሚጽፈው የእንግሊዘኛውን (የላቲን) ፊደላት ብቻ እንደሆነ ምኒሊክ ሲያጤኑ ወዲያውኑ ጥያቄ አነሱ።”

የወቅቱን ሁኔታው ስኪነር ሲገልጸው “ተግባራዊ የሆነው የንጉሠ ነገሥቱ አዕምሮ በቅፅበት ጥያቄ አመነጨ። የአማርኛ መፃፊያ (ታይፕ ራይተር) ስለምን ሊኖረን አይችሉም?.. ” ማለታቸውን ይገልፃል።

ሌላው የአሜሪካ ዘመናዊ የሪሚንግንተን አውቶማቲክ አዲስ ሞዴል ጠመንጃ ከታሸገበት ወጣ።በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ የሆነውንና ገና ገበያ ላይ ያልቀረበ መሳሪያ ሲቀርብላቸው ምኒሊክ አይናቸው በደስታ አበሩ።ብሏል ።

ዋናዎቹ ስጦታዎች እነዚህ ይሁኑ እንጂ ሌሎች ብዙ አይነት ስጦታዎች በግልና (የየቡድን ኦፊሰሮች)በአገር ደረጃ እንደቀረበላቸው በመፅሀፉ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪ ስኪነር ከአሜሪካን መንግሥት የግብርና መስሪያ ቤት ባለሙያዎች የተላኩ የጓሮ አትክልትና የአበቦች ዘሮች “ከሁሉም እጅግ ከፍተኛ ስጦታ ” ተብለው የተጠቀሱ ናቸው። ምኒልክም እነኚህን የጓሮ አትክልትና የአበባ ዘሮች በትልቅ ጥንቃቄ ለገበሬዎች እንደሰከፋፈሉና በውጤቱም እጅግ እንደተደሰቱ መስማቱን ስኪነር ገልፇል”።በማለት አቶ ንጉሴ አየለ ተካ በመፅሀፋቸው በገፅ 222/223 አብራርተዋል ።

እንግዲህ ምኒሊክ እነዚህን ስጦታዎችስ በደስታ ተቀበሉ።ለመሆኑ እሳቸው በአጸፋው ለአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት (ለአሜሪካን መንግስት)

 በወቅቱ ምን አይነት ስጦታ ላኩ?

በጽሁፉ መርዘም እንዳትሰላቹና ጊዜያችሁንም እንዳልሻማ ለሚቀጥለው ጊዜ አሳድሬዋለሁ።

መልካም የስራ ሳምንት ።

ቸር ይግጠመን