ከሰው ማሣ አትጨድ!

ተዋናይ ፣ አዘጋጅ ፣ ገጣሚ እና አርቲስት ፣
የጣይቱ የባህል ማዕከል በዋሺንግተን ዲሲ መስራች
አለም ፀሃይ ወዳጆ

ከሰው ማሣ አትጨድ!

ከሰው ማሳ አትጨድ …የንጥቂያ ከፍታ መሬት ታውላለች፤
እያንዳንዷ ውጤት …እያንዳንዷ ፍሬ ዋጋ አስከፍላለች፡
ጥረህ ግረህ ብላ …እንደ መፅሐፉ ቃል፡
ዛሬም ባይሆን ነገ የሰው ወዙ ያንቃል፤
አፈሩን ጎልጉሎ … ቆፍሮ አረስርሶ፡
ዘርቶ ተንከባክቦ ….ከእንቅልፉ ቀንሶ፤
ለዝናብ አንጋጦ ….ፀሐይን ተማልዶ፡
መዳፉን አሻክሮ …ልምዱን አዋሕዶ፤
በውኑም በእንቅልፉም ፡ሲያስብ ከርሞበታል፡
ፍሬው እስኪያፈራ ፡ ሥቃይ ቆጥሮበታል፤
ከሰው ማሳ አትጨድ ! …
በጨለማ ተገን ፤ እንዳይቀጨው አውሬ፡
እንዳያዳባየው ፡ ረግጦ ተራምዶበት
ግድ አይሰጠው ጥሬ …
አጥሮ ጠብቆት ነው ውጤት ሆኖ አብቦ ይህ ያየኸው ዛሬ፤
እያንዳንዷ ውጤት …እያንዳንዷ ፍሬ ዋጋ አስከፍላለች፡
ከሰው ማሳ አትጨድ …የንጥቂያ ከፍታ መሬት ታውላለች፤
ጥረህ ግረህ ብላ …እንደ መፅሃፉ ቃል፡
ዛሬም ባይሆን ነገ …. የሰው ወዙ ያንቃል፤
በግንባር ፡ በላብህ በጉልበትህ ጥረት ፡
በራስህ ተመንደግ በድካምህ ውጤት
ከሰው ማሣ አትጨድ…
ዝም ብሎ አላፈራም እንዲያው እንደዘበት … ዘለህ አትፈሰው…
ንቀህ ወይ ዘንግተህ የደከመበትን የፈጠረውን … ሰው ፤
በየቱም ሙያ መስክ …በምንም ሥራ ላይ
ደክመህ መመንደግ ነው … ከልብ የሚያረካው .. ስትውል ከበላይ
ጤና ተገብሮ ተስፋ ተሰንቆ ፡
በቁር በሐሩሩ …. ተጥሎ ተወድቆ፤
የጋሬጣ ፍቀት … ያደማ እሾህ ታልፎ ፡
የለማ ፍሬ ነው …ከዕድሜ ላይ ተቀርፎ ፤
ከሰው ማሣ አትጨድ !