ከመፃህፍት አለም ታላቁ ጥቁር ከተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ

መስፍን ጳውሎስ

ጀርመን ሙኒክ

ከታላቁ ጥቁር መፅሐፍ (ቅንጭብ)

ካለፈው የቀጠለ

ታላቁ ጥቁር ንጉሥ አፄ ምኒሊክ የዛሬ 116 አመት ከአሜሪካን መንግስት በጄ. ቆንስላ ስኪነር አማካኝነት የፕሬዘዳንቱን የግል ማስታወሻ ተጽፎ የተፈረመበት ፎቶግራፍ፣  ልዩ የሆነ በወቅቱ አዲስ ሞዴል ጠመንጃ  በተጨማሪም የተለያዩ የአትክልትና የተለያዩ የአበቦች ዘሮች እንደተበረከተላቸው ደራሲው  አቶ ንጉሴ አየለ ከተለያዩ በወቅቱ የተፃፉ ጋዜጦችንና ሌሎች ጽሁፎችን በመጥቀስ  አካፍለውናል።

 ታዲያ እንደምታስታውሱት  ያለፈውን ጽሁፍም ያቆምኩት የአቢሲኒያው ንጉሰነገስት አፄ ምኒሊክም ለአሜሪካን ፕሬዘዳንትና ለአሜሪካን መንግስት የላኩት የዘመኑ ስጦታ ምን ይሆን? በሚል ጥያቄ ነበር።

ደራሲው  „ታላቁ ጥቁር“በተሰኘው መፅሀፋቸው እንደሚከተለው የተርኩልናል።

„ዓርብ ዲሴምበር 25 ቀን ከሰአት በሇላ ምኒሊክ የመልዕክተኛው ቡድን ለአገሩ ፕሬዚዳንት ለቲዎዶር ሩዝቬልት የሚያደርሳቸው ስጦታዎች ተሰጡ።“

ሁለት ትላልቅ የዝሆን ጥርሶች ለሩዝቬልት በመታሰቢያነት እንዲደርሱ ተሰጡ።

የዝሆን ጥርሶቹ ዘጠኝ ጫማ ርዝማኔ ያላቸውና ወፍራሞች ነበሩ።

ሁለቱ በአንድ ላይ 384 ፓውንድ ክብደት ነበራቸው።

ከዚህም ሌላ ሁለት የአንበሳ ግልገሎች ለፕሬዚዳንቱ እንዲደርሱ በስጦታ ቀረቡ።…. „በማለት በገጽ 225 የቀረበ ሲሆን።

ደራሲው ለጆሮ አዲስ የሆኑ ታሪኮችን በሚያጓጓ አቀራረብ እንደ ማቅረባቸው ለምሳሌ ስለምኒሊክ ስጦታዎች በተለያዩ ገፆች ላይ ማስረጃ እየጠቀሱ አቅርበዋል።

ገጽ 362/3 ላይ በፎቶግራፍ በተደገፈ የቀረበው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል።

ስጦታዎቹ በመርከብ ተጉዘው ኒውዮርክ የነፃነት ሀውልት ያለበት ቦታ መድረሳቸውንና ስጦታውን በአደራ ተቀብለው ይዘው የመጡትን አሜሪካዊ የደስታ ስሜት ሲገልፅ እንዲህ ይላል።

„…. ሲመለስም ይኸው ሀውለት ስሜትን በሚነጥቅ ግርማ መለገሱ ተቀበለው። አንበሳውም ባለአደራውን ሚስተር ዌልስንን ተከትሎ „ከበረቱ“ ሲወጣ አስቀድሞ ብቅ ያለው ወደዚሁ የኒውዮርክ ምትሀታዊ ትዕይንት ነበር።ዓይኖቹ በጨዋነትና በኩራት ወዲያና ወዲህ አማተሩ። ጅቡ ግን አንገራገረ አፈትልኮ ከሚስተር ዌልስ ቁጥጥር ለማምለጥ አስቸጋሪ ሙከራ አደረገ።“ ይላል።

ከላይ ልገልጽ እንደሞከርኩት ሌሎች ጉዳዮችን ትተን ስለሰጦታዎቹና እንዴት እንደተጓጓዙ ፣በአጭሩ ከጉዟቸው እስከ አቀባበላቸውና የመጨረሻ ዕጣቸው ያለውን ስሜት የሚሰርቅ ወግ በዚህ ሁኔታ ማቅረብ የሚቻል አይደለምና ለማሳጠር እገደዳለሁ።

በመጨረሻም ለማሳረጊያ „The world NY“ የተሰኘው ጋዜጣ የዘገበውን እንመልከት ።

„ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች“ አዎን ይኸ የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል ነው።ቃሉም የምኒልክ ስጦታ በሆነው የክብር ጎራዴ (Honor of Sward) ላይ ተቀርጾ ቀድሞ ከአሜሪካ ገብቷል።አሜሪካም የነፃነት ችቦዋን ከፍ አድርጋ ወደ ሰማይ የዘረጋችበት ቃሉ ሳይሆን የመታሰቢያ ሀውልቱ በቆመበት ስፍራ ትይዩ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ „አምባሳደር“ የሆነው የምኒሊክ አንበሳ በተመልካቾች ፊት ጨዋነቱን ሲያስመሰክር ጅቡ ግን ሽብር ፈጠረ። „

በማለት መዘገቡን ደራሲው አሁንም በጋዜጣው ላይ march 18.1904 ያወጣውን ከዚህ ጽሁፍ በላይ የምትመለከቱትን ፎቶ አስደግፈው በገጽ 363 ላይ አስቀምጠዋል ።

አንባቢያን በአለፉት ጊዜያት ከ“ታላቁ ጥቁር“ መፅሀፍ በመቀንጨብ ያካፈልኳችሁ ከዛሬ 116 አመት በፊት የኢትዮጵያና የአሜሪካን የንግድና ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ጅማሮ፣የፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልትና የአፄ ምኒሊክ ስጦታዎች ታሪክ ስታነቡት ማርኳችሁ ከሆነ ጊዜያችሁን በከንቱ አላጠፋሁምና በእራሴና በእናንተ ስም ደራሲው አቶ ንጉሴ አየለን ከልብ አመሰግናለሁ ።

ቸር ይግጠመን።