123ኛው የአድዋ በአል አከባበር በሙኒክ ጀርመን

 የክብረ በዓሉ ስነስርአት የተጀመረው በሙኒክ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ምንዳ ጽጌ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ሲሆን የዘንድሮው የድልና የነጻነት ቀን ከወትሮው የተለዬ መሆኑን ሲያብራሩ ከሃያ ሰባት ዓመት ወዲህ የአድዋን ድል ስናከብር የነበረው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በቅኝ ገዢዎች የጭቆና መዳፍ ሥር ወድቀው ለሚማቅቁ የአፍሪካና የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ያበረከተውን ተምሳሌታዊ አስተዋጽዖ በሚመጥን መልኩ እንዳልነበር አጽንዖት ሰጥተዋል።ምክንያቱንም ሲያብራሩ መንግሥት የተከተለው ዘር ተኮር ፖሌቲካ በጋራ ኢሰቶቻችን ላይና በብሔራዊ አንድነታችን ላይ አሉታዊ ተጽአኖ እንዲያሳድር ተደርጎ ስለተቀረጸና ስለ ተሰራበትም ጭምር ነው ብለዋል።

የወቅቱን ሁኔታም አስመልክቶ በኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይና በወጣቱ ትውልድ መስዋእትነት የተገኘው የለውጥ ጉዞ ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት መሆኑን ሲያብራሩም ለውጡ እየተመራ ያለው በጥቂት ከእህዴግ በወጡ ለውጥ ፈላጊዎች የርእዮተ ዓለም ፣ የፖሊሲና የመዋቅር ለውጥ ሳይደረግ ፤ በተለይም ተጸእኖ ፈጣሪ የሆኑ መንግሥታዊ   ተቋማት በለውጡ ላይ አሉታዊ ተጸዕኖ  ላለመፍጠራቸው ዋስትና ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም እኛ ከሀጋራችንና ከሕዝባችን እርቀን የምንገኝ ዜጎች ለዚህ ለውጥ መምጣት ካሁን ቀደም ካበረከትነው አስተዋጽዖ  የላቀ ስለሚጠበቅብን በተናጥል ሳይሆን በጋራ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆን እንዳለብን አስገንዝበዋል ፡፡

 የዛሬውን 123ኛ የድልና የነጻነት ቀን ስናከብር መሰረታዊ ዓላማችን መሆን የሚገባው ታሪክን መዘከር ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰርተን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ መሆን አለበት፡፡ ከዛሬ 123 ዓመት በፊት ለውጪ ወራሪ ኃይል አልገዛም ብሎ ነጻነቱን በደምና በአጥንቱ ያስከበረ የኩሩ ዜጋ ልጆች ሆነን እያለ ዛሬ እኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጆችን መብት መቀዳጀት ተስኖን መታየታችን እጅግ ያሳዝናል ። አሁን በጅምር ላይ ያለው የለውጥ  አጋጣሚ እንደ ካሁን ብፊቶቹ  እንዳያመልጠን  አበክረን መስራት ይኖርብናል፡፡  በተገኙ አነስተኛ ድሎች ሳንዘናጋ የግል ሩጫን በመግታት በጋራ ለበለጠ ውጤት መነሳሳት አለብን፡፡  ከሁሉም በላይ ከሀገሩና ከወገኑ እርቆ የሚኖረውን ዜጋ ለማገልገልና አስተባብሮ ለሀገር ፋይዳ ያለው ተግባር እንዲሰራ ለማስቻል  በባእዳን አገር የሚቋቋሙ ኤምባሲዎች ኃላፊነትና ጊዴታ መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን መንግሥት ይከተል በነበረው የፖሊሲ ችግር የተነሳ ግንኙነታችን አንድ ወጥ እንዳልነበረ ግልጽ ነው ፡፡ ካሁን በቀላሉ የአመለካከት  ልዩንታችን ተከብሮ በዜጊነታችን ሁላችንም የዛች አገር ልጆች  መሆናችን ተረጋግጦ ፣ በአገራችን ጉዳይ ሁላችንም የሚያገባን በመሆኑ ግልጽነት ፣ ተጠያቂነትና ሁሉንም ያካተተ አሳታፊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን ያስፈልጋል ፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ኤምባሲያችን በባእድ አገር የሚትገኝ ትንሿ አገራችን መሆኗን ተገንዝበን በዜጊነት ማድረግ የሚገባንን ለማድረግም ሆነ እንዲደረግልን ለምንፈልጋቸው ጉዳዮች የጓሮ በር ሳያስፈልገን ህግና ስርአትን ተከትለን በዋናው በር እንደ ዜጋ እኩል እየገባን የመገልገል መብት እንዳለን መረዳት ይኖርብናል ብለዋል።

በመቀጠል አቶ አደራ ከበደ ስለ አድዋ ጦርነት መናስኤ ፣ ዝግጅት ፣ ሂደትና ውጤቱን አስመልክቶ ሙያዊ ትንታኔ ከነመረጃው አቅርበዋል ። ለጦርነቱ መነሻ ከሆኑ ምክኛቶች አንደኛው የአውሮፓ የቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት የጀመሩት እቅድ አካል መሆኑን የ1884-1885 የቅኝ ገዢዎች የጀርመን ኮንፍሬንስ ውሳኔ ማረጋገጫ ሲሆን እንደ መነሻ ሆኖ ያገለገለው የውጫሌው የውል ስምምነት አንቀጽ 17 የትርጉም ማጭበርበር ነበር ብለዋል ። ለጦርነት የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ኢጥልያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሳ የተከፋፈለ በመሆኑ በዘመናዊ መሳሪያ የታጠቅ 20 ሺህ የጣሊያን ሰራዊት የኣጼ ምንሊክን ሰራዊት በመደምሰስ ኢትዮጵያን በቀላሉ እንደሚቆጣጠር ገምቶ ነበር ነገር ግን አጼ ምንሊክ በጣም አስተዋይና ዜደኛ ስለነበሩ ከውስጥ የስልጣን ተፎካካሪያዎቻቸው ጋር የነበራቸውን ቅራኔ  በቅድሚያ አስወግደው በጋራ ፊታቸውን ወደ ውጭ ጠላት አዞሩ ። በሁለተኛ ደረጃ በስንቅና ትጥቅ አቅም በፈቀደ ጥሩ ዝግጅት ከማድረጋቸው ባሻገር የሰራዊቱን ጥራትና የሞራል ብቃት በጥሩ ሁኔታ አሳድገውት ነበር ። ሂደቱን አስመልክቶ ጦርነቱ የተመራው በራሳቸው በአጼ ምንሊክና በባለቤታቸው በንግሥት ጣይቱ ብጡል ብልህ አመራር ሲሆን የጦር ግምባር አመራሮችና የሰራዊቱ ጀግንነትና ብሔራዊ ፍቅር የላቀ መሆንና የመረጃ ልውውጥና ጥላትን በተሳሳተ መረጃ ማደናገር ዋና ዋና የሂደቱ የማእዘን ድንጋዮች  እንደነበሩ አጽንኦት በመስጠት አብራርተዋል ። ጦርነቱ የተደመደመው በኢትዮጵያ አሸናፊነት ስለሆነ ሀገራዊ ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው የላቀ ነበር ። አገራዊ ፋይዳው በዓለም ታሪክ ብቸኛዋ  በቅኝ ያልተገዛች ነጻነቷንና አንድነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር መሆኗን ያረጋገጠችበት ሲሆን  አህጉራዊ ጠቀሜታው ነጭ ገዢ ጥቁር ተገዢ ፣ ነጭ የበላይ ጥቁር የበታችና ተሸናፊ እንዳልሆነ የአድዋ ድል ተግባራዊ ማስረጃ መሆኑ በር ። ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነበር ይሄውም የቅኝ ገዢዎችን የአፍሪካ መቀራመት ህልም ቅዥት ማድረጉ ፣ ለዓለም ጭቁንና በቅኝ ገዢዎች አገዛዝ ለሚማቅቁ ሕዝቦች ተምሳሌታዊ አስተዋጽኦ እንደነበርው አስረድተዋል ። 

በማጠቃለያም አጼ ምንሊክ በአድዋ ድል የነበራቸውን ገድል ለማሳነስ የሚሞክሩ አንዳንድ ግለሰቦች እንደሚተርኩት ድሉ የእድል ወይንም የበለስ ምቅናት ጉዳይ ሳይሆን በወቅቱ የነበረውን የተፈጥሮ ችግር ተቋቁሞ በስንቅ ተደራጅቶ ለጦርነት ዝግጁ መሆን ፤ በወቅቱ የነበረውን የሥልጣን ሽሚያ በዘዴና በብልሀት አስወግዶ የውጭ ወራሪን ለመግጠም በአንድላይ መዝመት ፤ በዘመናዊ የጦር ስልትና መሳሪያ የታጠቀን የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ተዋግቶ ለማሸነፍ አጼ ምንሊክ ያደረጉት የሰራዊቱ የውጊያ ብቃት ፣ ከራሳቸው ከጣሊያኖች ሁሉ ሳይቀር ያገኙት የመሳሪያ ጥራት ፣ የጦር ሜዳ ውሎ የውጊያ ታክቲክ ፣ ስትራቴጂና የመረጃ ጥራት ውጤት  መሆኑን በመረጃና በአመክኒዮ ጭምር  በማብራራት ገለጻቸውን ቋጭተዋል።

123ኛው  የአድዋ የድልና የነጻነት በዓል በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪ ጊዜ የመንግሥት ተወካይ በክብር እንግድነት ጋብዘን ያከበርንበት ክብረበዓል ነው ። የተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ  ቆንስላ ጄነራል ተወካይና የዲያስፖራ ጉዳይ ዋና ኃላፊ አምባሳደር በረደድ አንሙት የክብር እንግዳችን በመሆን የተግኙ ሲሆን የበዓሉን ታዳሚ በኢትዮጵያ መንግሥትና በራሳቸው ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልእት በማስተላለፍ ነበር የጀመሩት ። በመቀጠልም የአድዋን ድል አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ መሰጠቱን በማስገንዘብ በቀጥታ በአገራችን ውስጥ ያለውን የለውጥ ህደት አስመልክቶ የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አስረድትው ለውጡ ያለመንም መንገራግጭ የሚከናወን ተግባር ሳይሆን ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት እልህ አስጨራሽ ጉዞ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል ። ከዚያም በተጨማሪ ለውጡ እንዲሰምር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ በተለይም ጥቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን የአንድ ዶላር በቀን እርዳታ በዲያስፖራ ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተግባራዊ እንዲያደርግ የተማጽኖ ጥሪ አቅርበዋል ።  አምባሳደር በረደድ አንሙት በውጭ አገር የምንኖር ዜጎች አገራችንን መርዳት የምንችለው በምናዋጣው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ የምንልከውን የውጪ ምንዛሪ በህጋዊ መንገድ ከላክን የውጪ ምንዛሪ እጥረትን በመቀነስ ረገድ ያለውን ፋይዳ በመግለጽ ትብብር እንድናደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪ ኤምባሲው እንደ ካሁን በፊቱ አንድ ቦት ብቻ ሆኖ አገልግሎት የሚሰጥ ሳይሆን ተገልጋዩ ዜጋ በብዛት ወደሚገኙባቸው ቦታዎች ተዘዋውረው መስጠት የጀመሩትን አገልግሎት እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል