ታሪክ ሰርቶ ማለፍ

በመስፍን ጳውሎስ  ውድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የማክበር ሰላምታችንን እያቀረብን በምንኖርበት በጀርመን አገር በሙኒክ ከተማ ኗሪ የነበሩትና የሀገራችን የኢትዮጵያን ታሪክ ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች በአለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች የማስተዋወቅ ስራ ለብዙ አመታት ሲሰሩ የነበሩት አቶ ግርማ ፍስሃ ዕድሜያቸው ደርሶ ጡረታ ሲወጡ ቀሪ ዘመናቸውን በሚወዷት ሀገራቸው እንዲሆን በመወሰን ከውድ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ሲኖሩ ቆይተው በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት እስከተለዩበት ድረስ ለሀገራቸው ባላቸው አቅምና ችሎታ የሚቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ በመቆየታቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል ። አቶ ግርማ ፍስሐ ስላደረጉት የሀገርን ማስተዋወቅ ስራ በአንድ ወቅት ከታዋቂው የሸገር ሬዲዮ „ስንክሳር“ የሚሰኝ ዝግጅት ላይ „የሙኒኩ ተንቀሳቃሽ ቤተመዘክር“ በሚል ርዕስ የቀረበውን ዝግጅት ምናልባትም ከጥቂቶች በቀር  ብዙዎቻችን የማናውቀውን የወንድማችንን የአቶ ግርማ ፍስሀን ከፊል የህይወት ጉዞ፣ዝርዝር ሥራዎችና የሀገራችን ታሪክ እንድናውቅ ይረዳል ብለው ያመኑ ሀገር ወዳድ ወገኖች ከሰጡን አስተያየት በመነሳት እኛም በሀሳቡ ስላመንበት የወንድማችንን ህልፈት የ40ቀን መታሰቢያ በማድረግ በኮሚዩኒቲያችን ስም ልናካፍላችሁ ወደናልና ከዚህ ጽሁፍ በታች የተቀመጠውን የድምጽ ማጫወቻ  በመክፈት እንድትከታተሉት በማክበር ጋብዘናችኋል። በዚህ አጋጣሚም አቶ ግርማ ፍስሀን በጀርመን አገር በሙኒክ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ነዋሪ ብዙዎች እንደሚያውቋቸው ግልፅ ነው። ነገር ግን ይህን ያህል ጠለቅ ብሎ ያደረጉትን እንቅስቃሴና ጥረት  ለሀገራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚያውቁ ምን ያህሉ ናቸው? በእውነትስ ብዙዎች „አብረን እንኖር ነበር እንጂ ለካ አናውቃቸውም ነበር! “ ሳያሰኛቸው ይቀራል? “ ብለን የአቶ ግርማ ፍስሀን ታሪክ መነሻ በማድረግ ሰፋ አድርግን አይተን የሚቀጥለውን ጥያቄ ለአንባቢያን እናቀርባለን በዓለም ዙሪያ በሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ኮሙዩኒቲዎች መሀከል የሚገኙ እንደ አቶ ግርማ ፍስሃ ያሉ ብዙ ቁምነገርን የሰሩ ልምድና ዕውቀቱ ያላቸው ወገኖችን አብሮ ከመኖር በዘለቀ ምን ያህል ጠለቅ ብለን እናውቃቸዋለን? ማንም ሰው ቀኑ ሲደርስ ያልፋልና ከማለፋቸው በፊትስ ታሪካቸውን፣ያደረጉትን ጥረትና የሰሩትን ስራ፣የፈፀሙትን ገድል እንዲያካፍሉን ዕድሉን እያመቻቸንላቸውስ ነው? ስንቶችስ ብዙ ነገር ሰርተው ታሪካቸው ሳይታወቅ ትውልድ ሳይማርበት እንደ ዘበት አልፈዋል?  የሚለውን ጥያቄ ይህ ጽሁፍ ለሚያነቡ ሁሉ በማቅረብ ውድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት በግልም ሆነ በተደራጀ መልክ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊወያዩበትና ሊንቀሳቀሱበት ይገባል እንላለን። በመጨረሻም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአቶ የግርማ ፍስሃን የረጂም ዘመን ለሀገር የተደረገ ጥረት ወንድማችን በህይወት እያሉ ቃለመጠይቅ በማድረግ አቶ ግርማ ፍስሀ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ታሪካቸው ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስቻሉትን የሸገር ራዲዮ „ስንክሳር „ዝግጅት አዘጋጅ ጋዜጠኛ መኮንን ወ/አረጋይንና ባልደረባውን ወንጌላዊት ብርሃኑን እንደተቋምም የሸገር ሬዲዮ ጣቢያን በሙኒክ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ስም ልናመሰግን እንወዳለን።የወንድማችንን ነፍስ ይማር!ለቤተሰቦቻቸው ፣ዘመድ ወዳጆቻቸው መፅናናትንና ጥንካሬን ይስጥልን!መልካም የማድመጥ ጊዜ እንመኛለን ።

» Weiterlesen