የአቶ ብሩክ ማሞ አጭር የሕይወት ታሪክ

2 Timothy 4:7-8 / 2ኛ ጢሞ 4 ፣ 7-8
Ich habe den guten Kampf gekämpft, den Lauf vollendet, den Glauben bewahrt; hinfort liegt für mich die Krone der Gerechtigkeit bereit;

መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥

I have fought the good fight, I have finished the race, I have kept the faith.

Henceforth there is laid up for me the crown of righteousness, which the Lord, the righteous judge, will award to me on that day

በወ/ሮ እናኑ ጌታሁን የቀረበ

ወንድማችን አቶ ብሩክ ማሞ ወይም በክርስትና ስሙ ተክለ አረጋዊ ሰኔ 6 ቀን 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። በአዲስ አበባ ቢወለድም የወጣትነት እድሜዉንና ትምህርቱን የተከታትለው በቀደሞ ስሙ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በአምቦ ክተማ ነዉ።

እንደማንኛውም ህጻን በዚያን ዘመን በቄስ ት/ቤ ፊደል ቆጥሮ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአምቦ ት/ቤት በጥሩ ሁኔታ ስላጠናቀቀ፣ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲሰ አበባ ጄኔራል ዊንጌት አዳሪ ት/ቤት ለመማር እድል አገኝቶ ለ4 ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሏል። በጥሩ ውጤትም አጠናቋል።  

ብሩክ የማትሪክን ፈተና 4 A ና 4 B በማምጣት ከግርማዊ ጃንሆይ እጅ በስማቸው የታተመ ን.ነ.ቀ.ኃ.ሥ የሚል ሜዳልያ ለመሸለም በቀቷል።  

ቀጣይ ትምህርቱንም በዘመኑ ዝነኛ ወደነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በመቀላቀል ተከታትሎ በጥሩ ውጤት በማጠናቀቁ፣ በእጩ መኮንንነት ደረጃ ሲመረቅ በጊዜው ከነበሩት መሪ ፕሬዜዳንት ጄኔራል ተፈሪ በንቲ እጅ ሽልማት ለመቀበል በቅቷል።

ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ቀድሞው ዮጎዝላቪያ ተልኳል። እጩ መኮንን ብሩክ ወደ አውሮፓ የመጣበት ጊዜ ክረምት ስለነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓን ብርድና የበረዶ ክምር የተጋፈጠበት ጊዜ እንደነበር በየአጋጣሚው ሲናገር ይደመጥ ነበር።

በትምህርት ላይ እንዳለም በወቅቱ ተማሪው የሃገሩን እጣ ፋንታ በንቃትና በመደራጅት የሚሳተፍበት ዘመን ነበረና የፖለቲካ ትግሉን ተቀላቀሎ ተሳትፎውን ቀጠለ። ብሩክ በፖሎቲካ አቋሙ ፍጹም የማይደራደር፣ በግልጽና በድፍረት አብረውት ከነበሩት ከደርግ ከፍተኛ መኮንኖችና ባለስልጣናቶችም ጋር በዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ በግንባር የሚፋለም ነበር።

ተራማጁ ኃይል እርስበርሱና በኋላም ሙሉ በሙሉ በደርግ የተመታበት ወቅት ነበርና ውጭ ሀገር በትምህርት ላይ የነበሩና በአቋማቸው የፀኑ ተማሪዎች፣ መንግሥት በሚያደርገው ተፅዕኖ ምክንያት ትምህርታቸዉን ሳያጠናቅቁ ወደ ኢትዮጵያ እየተጠሩና ችግር ዉሰጥ እየገቡ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ከትምህርት ገበታቸው በመነሳት ወደ 3ኛ ሃገር ለስደት ተዳርገዋል። ብሩክም እነደዚሁ ወደ ጀርመን ለመሰደድ ተገደደ። 

በስደት በነበረበት ጊዜም ቢሆን ለሀገሩና ለወገኑ እንቅልፍ አልነበረውም። የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ሙኒክን በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር በሙኒክ፣ እንዲቋቋም አሻራውን አስፍሯል፣ በአመራር አካልም ውስጥ ተሳትፏል። በቅንጅት ደጋፊ ድርጅትም ውስጥ እንደዚሁ።

ብሩክ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ፣ ጨዋነት ሁልጊዜ የማይለየው የውይይት ሰው ነበር። አንባቢና ሰፊ የእውቀት አድማስም ነበረው። 

በመራራውና እልህ አሰጨራሹ የዲሞክራሲና የፍትህ ትግል ዉስጥ በECADF Current Affairs ቤት ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው። ቤቱን ከመቆርቆር ጀምሮ ትግሉን መልክ ከሚያሲዙ አንጋፋ አድሚን መካከል የነበረና Hizeb Balew በሚል ስምም የሚታወቅ ነበር።  

ፍቅር በተላበሰ ግሳፄ እየተቆጣ፣ ሀገር መውደድ ምን እንደሆነ ለተረካቢው ትውልድ ያስተምር እንደነበረ፣

ወጣቱን ትውልድ ስለ ሀገሩ ታሪክ እንዲያዉቅና ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ መፅሐፍትን እያነበበ ጭምር ትውልድን የሚያስተምርና የሚቀርፅ ብርቱ መምህር እንደንበረ ሰሞኑን የምናነባቸዉ መልእክቶች ይመሰከራሉ።

ከለውጡ ወዲህ፣ ካለፈው ሁለት አመት ጀምሮ በውጪ የሚኖሩ ተቃዎሚ ወገኖች ወደ ሃገራቸው በሚገቡበት ጊዜ እሱም ከሀገር ከወጣ በ45 ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትውልድ ሀገሩ ለመሄድ በቀቷል።

አሁንም ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ በሄደበት ጊዜ በአደረበት ድንገተኛ ህመም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን!

ስርዐት ቀብሩም ባለፈው ሳምንት Nov 8/2020 ወይም በኢትዮጵያ ጥቅምት 29 /2013 ውድ ቤተሰቦቹ በሚኖሩበትና የወጣትነት እድሜውን ባሳለፈበት በአንቦ ከተማ በደብረ ብርሃን እየሱስ ቤ/ክርስትያን ውስጥ ተፈፅሟል።

የወንድማችን ብሩክ ማሞ ህልፈት ድንገተኛ ቢሆንም ነገን ሳይጠብቅ፣ ደከመኝ ልረፍ ሳይል፣ በአመነበት አስተሳሰብና በነበረው አቅምና ችሎታ ያለውን የሰጠ፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚችለውን ሁሉ በማድረግ፣  እንደ ዜጋ የበኩሉን ያበረከተና ያለፈ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው! 

ለሀገሩና ለባንዲራው የነበረው ፍቅርና ክብር ከፍተኛ ነበር! በመሆኑም እነደተመኘውና እንደናፈቀው  የመጨረሻ ሰዓቱም በሚወዳት ሀገሩና በሚወዳቸው ወገኖቹ መካከል ሆኖ የመጨረሻውን የሞት ፅዋ ቀመሰ!

ወንድማችንና ሀገር ወዳዱ ብሩክ!

ስትደክም፣ ስትባክንና ስትሮጥ ሕይወትህን አሳለፍክ፣ ዛሬ በድንገት ባልታሰበ ጊዜና ቦታ በሞት ተለየኸን!  „በዘርና በጎጥ ሕዝቡ ተከፋፍሎ ማየት ደስ አይልም፣ ቶሎ እመለሳለሁ“ እያልክ እንደቀልድ ለእረፈት እንደሄድክ ላትመለስ በዚያው ቀረህ!

የደከምክበትንና የታገልክለትን የነፃነት አየር በበቂ ሳትተነፍስ በቅፅበት ወደ ዘለዓላማዊው እረፍት በመሰናበተህ አዝነናል!

አንተ ግን ሩጫህን ጨርሰሃልና እረፍ!  

ፈጣሪ ነፍስህን በአፀደ ገነት ያኑርልን! 

ለልጁ ለመሰከረም፣ ለቤተሰቡ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ጓደኞቹ፣ አንዲሁም ለሙኒክ የኢትዮጵያውያን ማሕበረሰብ በሙሉ መፅናናትን ይስጥልኝ።

November 15, 2020


ማስታወሻ ከኤፍሬም ገ/ጻዲቅ

ቀኑንና ሰዓቱን በትክክል በማላስታውሰው ለስደቱም ለሃገሩም ኣዲስ በነበርኩበት በመጀመሪያው አመት በኣንደኛው ቀን ያኔ አንኖርበት በነበረው መጠለያችን የሚያውቃቸውን ሰዎች ሊጎበኝ በመጣበት ወቅት ነበር ብሩክን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት።

      ከሰው ጋር ለመግባባት ብዙ የማይከብደው ብሩክ ከታናናሾቹም ጋር ቢሆን ዝቅ ብሎ ስቆና ተጫውቶና ቀልዶ ወድያው ጉዋደኛ የሚሆን ሰው ወዳድ እና ወገኑን ኣፍቃሪ እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ ኣልወሰደብኝም።

በተለይ እኔንና እኔን መሰል በሙኒክ ከተማ ዉስጥ በቀላሉ የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት አድል ያልነበረን ኣአዎች በዚህ ኣገር ቀደም ብለው የመጡና ከኛ በተሻለ የሃገሩን ሁኔታ የሚገነዘቡ እንደ ብሩክ ያሉ አህትና ወድሞቻችን ከጠበቃ አስከ ፍርድ ቤት የቓንቓ ትርጉምና አርዳታ በማድረግ ልደረጉልን ወገናዊ ትብብር ምን ግዜም አናከብራጨዋለን።

   ወንድምስችን ብሩክ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን ለመርዳት ካደረጋቸው የተለያዩ ተግባራቶች ዉስጥ በቅርብ ልመሰክርለት የምችለውን አንኩዋን ባነሳ በሙኒክና ኣካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር (ኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ)አንዲጠናከርና ኢትዮጵያውያን ህብረትና ትብብር አንዲኖረን ያደረገው ኣስተዋጽዎ ዋነኛው ነው ።

   ሁላችንም አንደምናውቀው በሙኒክ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር ኣለ ሲሉት አየጠፋ ጠፋ ሲሉት አየኖረ በብዙ ዉጣውረድ ከዚህ የደረሰ ማህበር ነው ።

  በተለይ ብሩክ በስራ ኣስኪያጅ ኮሚቴ ኣባልነት የማህበሩ ጸሀፊ ሆኖ ያገለገለበት የስራ ኣመራር ኮሚቴ የማህበሩን ህልውና ማስቀጠል በተሳነው ወቅት ብሩክ ብቻውን አንደ ኣንድ ኮሚቴ በሱ በኩል ለሚመጡ ደብዳበዎች መልስ አየሰጠ በሌላ በኩል በግል የሚያውቀንን ሰዎች ማህበሩን አንድናስቀጥል አያግባባና አያበረታታ በጣም ባለቀ ሰኣት የኣባላትም ቁጥራቸው በተመናመነበት ኣስቸጋሪ ግዜ ተረካቢ ኮሚቴ በማስመረጥ ከለሎቹ የኮሚቴ ኣባላት ጋር በመተባበር የማህበሩን ህልውና ያስቀጠለ ባለውለታችን ነው።

  አኔ በቅርበት ያየሁትን መሰከርኩለት አንጂ ብሩክና ኢትዮጵያዊነት በፍጹም የማይለያዩ  የለት ከለት ክስተቶች አንደነበሩ ብሩክን የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል።

 በታሪክ ኣዋቂነቱ በባንዲራ ወዳድነቱ በሰው ኣክባሪነቱና ቁምነገርኝነቱ የምናውቀው ብሩክ ዛሬ በህይወት ቢለየንም ባከናወናጨው ተግባራቱና በወንድማዊ ፍቅሩ ምን ግዜም በልባችን ይኖራል።

በመጨረሻም ኣምላክ የውንድማችንን ነፍስ በገነት ያኑርልን አያልኩ ዝክረ ብሩክ ማሞ መታሰቢያ ጦንልኝ ዘንድ ይቺን  ኣጭር ስንኝ ኣበርክቼለታለሁ።

የወንድማችንን  አቶ ብሩክ ማሞን ዜና እረፍት አስመልክቶ በሙኒክ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ አስተባባሪነት
በተዝጋጅው የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ የቀረቡ  ግጥሞች።


Dieses Bild hat ein leeres Alt-Attribut. Der Dateiname ist 17.11.pngDieses Bild hat ein leeres Alt-Attribut. Der Dateiname ist bruk.jpeg

ኤፍሬም ገብረጻድቅ


ዞሮ ዞሮ ከቤት
ኖሮ ኖሮ መሬት
አንዲል የኣበው ወጉ
የተፈጥሮም ህጉ
ሃዘኑ ቢከፋም መለየቱ ከብዶ
ዘላለም ኣይኖርም ሰው ከሰው ተዋዶ
ከሎረቱ መንደር ኣምቦ ነው አድገቱ
ብሩክ ሁን ተባረክ ያለችው አናቱ
ቃል ያለው ለምድሩ ለባንዲራዪቱ
ተግባሩም ይህ ነበር አስከለተ ሞቱ
ቃሉን ሳያሳንስ ውሉን ሳይስት ደርሶ
ሃገሬን እዳለ ሄዷል ተመልሶ
አፈርሽ አፈሬ ብረሳሽ ሞት ይርሳኝ
አርባአምስ አይደለም ሺ አመትም ይግፉኝ
በልቤ ማህተም ያተምኩሽ እናቴ
መጣሁ ተቀበይኝ ይህ ነበር ምኞቴ
ሩጫዬም በቅቷል ጉዞዬም ተገቷል
የተስፉ ብርሃን በሃገሬ ላይ በርቷል
እንግዲህ ትውልድ ሆይ ቀንዲሉን አደራ
እንደ ጥንቱ ሆነህ በፍቅር በጋራ
ሃገርክን የወላድ መካን ካላረጝካት
ያኔ ነዉ የኔ ነፍስ ሃሴት የሚያረካት
አዎ ብሩክ ህልሙ አረንጏዴ ቢጫ ቀይ ነዉ ቀለሙ
ይሄንን እያየሁ
ሌላ ምን እላለሁ
ዞሮ ዞሮ ከቤት
ኖሮ ኖሮ መሬት
ይህንን አውቃለሁ።


 

አንበሳዬ
መስፍን ጳውሎስ
Nov. 14 /2020 ሙኒክ

 በጣም ቀረብ ብሎ ውስጥ አዋቂ ሆኖ ፡
ትውልድና እድገቱን ሙያና ትምህርቱን ዘርዝሮ ባያውቅም ፡
ዝምድና ባይኖረው ቤተስብ ባይሆንም ፡
ብሩክን ለማወቅ ብዙ ጊዜ አይፈጅም።
የሃገር ጉዳይ የወገኑ ስቃይ እረፍት የማይሰጠው ፡
ትንሽ ረጋ ብሎ ላየ ለታዘበው ፡
ብሩክ ላገር እንጂ ለራሱ ግድ የለው፡፡
በሙኒክ ከተማ አብረን በኖርንበት ፡
ባለፉት 30 የስደት አመታት ፡
እኔ ያስተዋልኩት ከብሩክ ባህሪያት ፡
ለሁሉም ወገኑ ሳያደርግ ልዩነት ፡
ሰላምታው ሞቅ ያለ ከውስጣዊ ስሜት ፡
“አንበሳዬ!” ብሎ እቅፍ የሚያደርጋት ፡
እንደ አንድ ዜጋ፣እንደ አንድ ኗሪ ወንድም ነው ያጣሁት!፡፡
ብሩክ በባህሪው ፡
ትንሹን ትልቁን ሁሉን አክባሪም ነው ፡
የማስመሰል ሳይሆን ከውስጡ የሚፈልቅ የሰው መውደድ አለው ።
እኔ እስከማውቀው እኔ እንደታዘብኩት ፡
ብሩክን ውቀሱት ብሩክን ዝለፉት ፡
ይህ አያስቆጣውም አታዩም መከፋት ፡
ግን! ግን! ብቻ ባይኑ ብሌን ባገሩ አትምጡበት!
ለፍቶ ያሳደገውን፣ ደክሞ ያስተማረውን፣ ያን ደሀ ወገኑን ፈጽሞ አትንኩበት።
ያኔ ይበሳጫል! ቁጭት ይሰማዋል! ያንገበግበዋል!
አንበሳዬ ይቆጣል!!
በሃገር ምስቅልቅል ፈተና ጊዜያት ፡
በሃዘን በደስታ ወገን ለወገኑ መቆም ሲኖርበት ፡
ብሩክ አይታጣም ኢትዮጵያን ያሉ ዕለት ፡
ሃገሬን ያሉ ዕለት ፡
ባንዲራዋን ለብሶ ብቅ ይላል በኩራት ፡
ያኔ ነው ብሩክን አንበሳዬን ማየት።
ሌላው የብሩኬ አቅምና ክህሎቱ ፡
ላመነብት ጉዳይ ጸንቶ መቆሙና ሌት ተቅን መስራቱ ፡
ወገን ማሰባሰብ የማደራጀቱ ፡
ምስክሮች ናቸው በተግባር የታዩ ማህበር ተቁማቱ ።
ለማስረጃም ያህል ለመጥቀስ ብንሞክር ፡
በዚህ በከተማ የኢትዮጵያውያን ቁጥር
እንዲህ እንዳሁኑ ሳይበዛ ሳይጨምር ፡
ወገን ለወገኑ በደስታ ሃዘኑ አብሮ እንዲተባበር ፡
ይህ የእኛ የኢትዮጵያ መረዳጃ ማህበር ፡
ገና ከጥንስሱ ሀ ብሎ ሲጀመር ፡
ከመስራቾቹ ውስጥ ብሩክ አንዱ ነበር።
ብሩክ!
ለሰራኽው ስራ ክብር ልንሰጥህ ፡
ለዋልከው ውለታ ልናመሰግንህ ፡
ምንም ባንታደል በህይወት እያለህ ፡
ተጽፎ ይኖራል ገድልና ታሪክህ።
ሃገሬን አትንኩ! ወገኔን አትንኩ! ብለህ በመጮህህ
ለወገን ኖረሃል ሳትኖር ለራስህ!
አንበሳችን ሆነህ!
እድሉን ካገኘሁ ለመዘከር አንተን፡
እንዳንተ ቁም ነገር ሰርተው ያለፉትን ፡
ይህንን ማህበር ለዚህ ያበቁትን ፡
የቀድሞ ጓደኞች ባልደረቦችህን ፡፡
በዚህ አጋጣሚ እንድናስባቸው ፡
ይዘርዘር፣ይዘከር ይጥራ ስማቸው ፡
ወገን ይወቃቸው !!ወገን ያስታውሳቸው!፡፡
በሙኒክ ከተማ የሚኖረው ወገን
በክፉም፣ በደጉ አንድ ላይ እንዲሆን
ከልብ አስባችሁ ከልብ ተጨንቃችሁ
የህብረት መሰረት ምሶሶ ያቆማችሁ
ዛሬ መሃላችን በህይወት የሌላችሁ
እነሆ ይጠራ ደማቁ ስማችሁ።
ውድ ውንድሞቻችን ፍቅሬ በርጋንና ሳምሶን ጌታሁን ፡
ዶ/ዘውዱ እንግዳ፣መንግስቴ አብበን ፡
ከእህቶቻችንም ገነት ጳውሎስና ዘውዴ አድማሱን
ምንም በየተራ ባካል ቢለዩን ፡
ከቶ አንረሳቸውም ውለታ አለብን ።
ምክንያት ስለሆኑ ለዛሬው አንድነት፣ላብሮነታችን፡
እሱ ፈጣሪያችን ነፍስ ይማርልን።
እንግዲህ ለሃገሩ የኖረ ሲድክም 
ተፈጥሮ ነውና በህይወት ቢለዩንም
ከድካም በሁዋላ አረፉ ነው እንጂ ሞተዋል አንልም።
ስለዚህ ብሩኬ የእኛ አንበሳችንም፡
ሲደክም ሲለፋ የኖረ ቢሆንም፡
ድንገት ሳናስበው ማለፉን ብንሰማም ፡
ብሩክ አረፈ እንጂ ተራ ሞት አልሞተም።
ነፍስ ይማር!
ወድ ወንድማችን ብሩክ ማሞ እንወድሃለን፣እናከብርሃለን!
ለልጁ ለመስከረም ብሩክና ለቤተሰቡ፣
ለሙኒክ ማህበረስብና ወዳጅ ዘመዶቹ ፈጣሪ መጽናናትንና ጥንካሬን እንዲሰጥ እንመኛለሁ።

ዮናስ (ኡጁሉ)

የሰው ልጅ በበጎ ተግባሩ
ለስራው ላገሩ
ቢታወስ በጥሩ
መልካም ግንዛቤ ይሰጣል ለዛሬ
በተግባር የሆነ የታየበት ፍሬ
ና እንመካከር
ተጨንቃለች ሐገር
ድምፅ እንሁንለት ድምጽ ለታፈነ
ትለኝ የነበረው ትዝታው አልበነነ
ሩጫህ ድካምህ
ለሕዝብህ
ለአገርህ
የምር ነበረ የቆሰለ ልብህ
በሚያምረው ቁመናህ በሐገርህ ባንዲራ
አሸብርቀህ ወጥተህ ሰልፍ ሰትመራ
ከሙንሽን ሰው ጋራ
ግፈኞች ሳትፈራ
ሕዝብ ባለው ብለህ ሰታታግል ኖረህ
ተቆጭተህ አምርረህ
ፍሬውን አይተኸው የድካምኸን ዋጋ
አገርህ ብትገባ ሠላም ልታወጋ
የጠማህን ሠላም ቡዙም ሳትጎነጭ
አንደ ደከምክላት በደስታ ሳትፈነጭ
ትንፋሽህ መቆሙን መርዶ ስንሰማ
አዘንን ተከፋን ልባችንም ደማ
ይስማኛል ድምፅህ ዛሬም ትኩስ ሆኖ
ይታያል አንገትህ ባንዲራ አጀብኖ
ና እንመካከር
ተጨንቃለች ሐገር
ብለህ ስትጣራ
የልፋትህ ውጤት መና ሆኖ አልቀረ
ይኸው በጬኸትህ ሁሉ ተቀየረ
ድል አይተህ አልፈሃል በቅድሰቷ ምድር
በአገርህ በክብር
ለሐገር አፈር በቃህ ይኼም መታደል ነው
የኛን ጌታ ይወቀው
ና እንነጋገር ያዝና ባንዲራ
ሐገር ተጨንቃለች ገብታለች መከራ
በለህ የምትጠራኝ
ሁሌ ነው ሚሠማኝ
ሐዘንህ ነክቶኞል በክፉ በፀና
ነፍስ ይማር ጋሽዬ ያኔ ክቡር ጀግና
ሐዘኑ በርትቶ በውስጣችን ቢቀር
ብሩክ ማሞ ሚለው ስምህ አይቀበር
ና እንመካከር
ተጨንቃለች ሐገር